የቻይናው መሪ ዢ ዢንፒንግ እና የሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ስላለው ጦርነት እና በሌሎች “ዓለም አቀፋዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች” ዙሪያ በሳምንቱ መጨረሻ እንደሚወያዩ ክሬምሊን ገለጸ።
መሪዎቹ በኡዝቤኪስታን የሚወያዩ ሲሆን ለምዕራቡ ዓለም “አማራጭ” በሚያሳየው ስብሰባ ላይ ነው የሚገናኙት ብሏል ክሬምሊን።

ዢ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ የመጀመሪያውን የባሕር ማዶ ጉብኝታቸውን እያደረጉ ነው።
ጉብኝቱ ዢ ሦስተኛ የሥልጣን ዘመን ለማግኘት በሚጥሩበት እና ፑቲን ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላቸው ግንኙነት በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ዝቅተኛ ደረጃ በደረሰበት ወቅት የሚካሄድ ነው።
ዢ የሦስት ቀን ጉብኝታቸውን በካዛኪስታን ረቡዕ ጀምረዋል።
ከዚያም ለሁለት ቀናት በሚቆየውና በሳምርካንድ በሚካሄደው የሻንጋይ የትብብር ድርጅት (ኤስሲኦ) ስብሰባ ላይ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ይገናኛሉ።
ፑቲን ከሕንድ፣ ከፓኪስታን፣ ከቱርክ እና ከኢራን መሪዎች ጋርም ይገናኛሉ።
ከቻይናው መሪ ጋር የሚያደርጉት ውይይት “በተለየ መልኩ ጠቃሚ ነው” ሲሉ የክሬምሊን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቃል አቀባይ ዩሪ ኡሻኮቭ ተናግረዋል።
ጉባኤው እየተካሄደ ካለው “ትልቅ የፖለቲካ ለውጥ ጀርባ የሚደረግ ነው” ብለዋል።
ኤስሲኦ እአአ በ2001 ከቀድሞ የሶቪየት ማዕከላዊ እስያ አራት አገራት ጋር የተመሠረተ ነው።
ቻይና እና ሩሲያ ድርጅቱን ለምዕራባውያን ቡድኖች እንደ አማራጭ ለማቀረብ ደፋ ቀና ሲሉ ቆይተዋል።
የዢ ጉብኝት ዜሮ ኮቪድ የተባለው ፖሊሲ በቀጠለበት እና በቻይና በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት ወቅት ነው።
የተቀረው ዓለም ከቫይረሱ ጋር አብሮ መኖርን በመማር ወደ ቀድሞ ሕይወት ሲመለስ ቤጂንግ ድንገተኛ ሁኔታ በተፈጠረ ቁጥር ሁሉንም ከተሞቿን እና ግዛቶችን መዝጋቷን ቀጥላለች።
ዢ ለመጨረሻ ጊዜ ከአገር ውጭ ጉብኝት ያደረጉት እአአ ጥር 2020 ምያንማርን ለመጎብኘት ሲያቀኑ ነው።
ይህም የመጀመርያው የእንቅስቃሴ ገደብ በውሃን ከመጣሉ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ነበር።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቻይና ለመቆየት የተገደዱ ሲሆን ሐምሌ ላይ ከዋናው ቻይና ውጭ ወደ ሆንግ ኮንግ አቅንተዋል።
ፑቲንም በውጭ አገራት ያልተለመደ ጉዞ እያደረጉ ነው።
የሩሲያ ወታደሮች ዩክሬንን ከወረሩ በኋላ በሐምሌ ወር ቴህራን ላይ ከቱርክ እና ከኢራን መሪዎች ጋር ካደረጉት ስብሰባ ወዲህ ይህ ሁለተኛው የውጭ ጉብኝታቸው ነው።
ሁለቱ መሪዎች በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ ነው የሚገናኙት። ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በየካቲት ወር ቤጂንግ ባዘጋጀችው የክረምት ኦሊምፒክ ነው።
በየካቲት የተካሄደውን ስብሰባ ተከትሎ ሁለቱ መሪዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ በአገሮቻቸው መካከል ያለውን ወዳጅነት “ገደብ የለሽ” ብለውታል።
ሩሲያ ከቀናት በኋላ ዩክሬንን ወረረች። ቻይና ወረራውን ማውገዟንም ሆነ መደገፏን አልገለፀችም።
ቤጂንግ ለጦርነቱ ተጠያቂዎቹ ሁለቱም ወገኖች ናቸው ትላለች።
ቻይና በሩሲያ ላይ የተጣለው ዓለም አቀፍ ማዕቀብ አካል አይደለችም። በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥም እያደገ መሄዱን ቀጥሏል።
ከዩክሬን ወረራ በኋላ ሕንድ እና ቻይና ከሩሲያ የሚያስገቡት ነዳጅ ጨምሯል።
ቻይና ከምዕራቡ ዓለም እና በተለይም ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት በቅርብ ወራት ወዲህ ውጥረት ነግሦበታል።
የታይዋን ጉዳይ ደግሞ ነገሩን አባብሶታል። ቻይና ደሴቱን የግዛቴ አካል ነው ትላለች።
የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ደሴቲቱን መጎብኘታቸውን ተከትሎ “ምላሽ ለመስጠት” በሚል ቤጂንግ በታይዋን ዙሪያ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ወታደራዊ ልምምድ አድርጋለች።
የቻይናን ጉዳይ የሚከታተሉ ባለሙያዎች እንደሚሉት በእንቅስቃሴ ገደብ እና ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ምክንያት ተግዳሮቶች ቢኖርባቸውም፣ ዢ ከሁለት ዓመት በኋላ ቻይናን ለቀው ለመውጣት መወሰናቸው በአመራሩ ላይ ያላቸውን እምነት ያሳያል።
ተንታኞች እንደሚሉት በመጪው ጥቅምት በሚካሄደው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ኮንግረስ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ለሦስተኛ ጊዜ እንዲመረጡ ይጠብቃሉ።
የሻንጋይ የትብብር ድርጅት ማነው?
ኤስሲኦ በቻይና፣ ሩሲያ፣ ካዛኪስታን፣ ኪርጊስታን፣ ታጃኪስታን እና ኡዝቤኪስታን የተመሠረተ የአውሮፓ እና እስያ አገራት የፖለቲካ ፣ የምጣኔ ሀብት እና የደኅንነት ድርጅት ነው።
ኢራን በ2001 የተቋቋመውን ድርጅት ለመቀላቀል ፍላጎት አላት።
ቻይና በቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክቶቿ በቀጠናው ትልቅ መዋዕለ ንዋይ የምታፈስ ሲሆን አባላቱ በንግድ ዙሪያ ይወያያሉ።
ቤጂንግ ከአውሮፓ ጋር ለምታደርገው የንግድ ልውውጥ አዳዲስ የባቡር መስመሮችን ለመዘርጋት የምትፈልግ ሲሆን የመካከለኛው እስያ አገራት ደግሞ ከቻይና ጋር የበለጠ ግንኙነት ለመፍጠር ጉጉት አላቸው።
ኪርጊስታን በ2023 ከቻይና እና ኡዝቤኪስታን ጋር የሚያገናኛትን አዲስ የባቡር መስመር ዝርጋታ እንደምትጀምር አስታውቃለች።
