በዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ ሥርዓተ ቀብር ላይ የቻይና መንግሥት ተወካዮች እንዲገኙ የቀረበው ግብዣ እንዲሰረዝ የዩናይትድ ኪንግደም ፖለቲከኞች እና የምክር ቤት አባላት ጠየቁ።
የቻይና መንግሥት ተወካዮች በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዲገኙ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መንግሥት መጋበዛቸው አሳስቦናል በማለት ለአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ደብዳቤ ከጻፉት መካከል የወግ አጥባቂው ፓርቲ ጉምቱ አባላት ይገኙበታል።
የምክር ቤት አባላቱ በቻእና አነሳ በሆኑት ዊገር ሙስሊም ማኅብረሰብ አባላት ላይ “የዘር ማጥፋት” ወንጀል የሚያስጽሙት ባለሥልጣንት መጋበዛቸው አሳሳቢ ነው ብለዋል።
የፊታችን ሰኞ መስከረም 09/2015 ዓ.ም. በሚከናወነው የንግሥቲቱ ሥርዓተ ቀብር ላይ እንዲገኙ ለቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ይፋዊ ጥሪ የቀረበ ቢሆንም ፕሬዝዳንቱ ግን ይገኛሉ ተብሎ አይጠበቅም።
ፕሬዝዳንቱ በዚህ ሳምንት ከሁለት ዓመታት በኋላ በመጀመሪያቸው በሆነው የውጭ አገር የሥራ ጉብኝት ጉዟቸው ወደ ካዛኪስታን እና ኡዝቤኪስታን አቅንተዋል።
የቻይናው ‘ሳውዝ ቻይና ሞርኒን ፖስት’ ጋዜጣ ዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ምክትል ፕሬዝዳንት ዋንግ ኪሻን ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በንግሥቷ ቀብር ላይ ማን ይገኛል?
በንግሥቲቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ወደ 500 የሚጠጉ ርዕሳነ ብሔራት እና የውጭ አገር ተወካዮች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አብዛኞቹ መሪዎች በንግድ አውሮፕላን በረራዎች እንዲመጡ የተጠየቁ ሲሆን፤ ምዕራብ ለንደን ከሚገኝ ቦታ በአውቶብስ እንደሚጓጓዙም ተነግሯቸዋል ተብሏል።
በዕለቱ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከሚገኙት መካከል ከመላው አውሮፓ የሚመጡ ንጉሣውያን ቤተሰብ አባላት ይገኙበታል።
የቤልጂየም፣ የኔዘርላንድስ፣ የስፔን ነገሥታት የሚገኙ ሲሆን፣ የኖርዌይ፣ የስዊድን፣ የዴንማርክ እና የሞናኮ ንጉሣውያን ቤተሰቦችም በቀብሩ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
ከአገራት መሪዎች መካከል የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከእነ ባለቤታቸው በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደሚገኙ ዋይት ሐውስ አረጋግጧል።
ከኮመንዌልዝ አገራት መሪዎች መካከል የአውስትራሊ፣ የካናዳ እና የኒው ዚላንድ ጠቅላይ ሚንስትሮች ጥሪውን ተቀብለዋል።
የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የፈረንሳይ፣ የደቡብ ኮሪያ፣ የብራዚል እና የቱርክ ፕሬዝዳንቶችም እንደሚገኙ ይጠበቃል።
ያልተገባዙትስ እነማን ናቸው?
ከሩሲያ፣ ከቤላሩስ እና ከሚያንማር በዩናይትድ ኪንግደም ንግሥት የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዲገኙ የተጋበዙ ባለሥልጣንት የሉም።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በንግሥቲቱ ቀብር ላይ የመገኘት ዕቅድ እንደሌላቸው ቃል አቀባያቸው ቀደም ሲል ተናግረው ነበር።
ዩናይትድ ኪንግደም ከሶሪያ፣ ከቬንዙዌላ እና ከአፍጋኒስታን ጋር ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስለሌላት ከእነዚህ አገራት በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚገኝ አይኖርም።
ሰሜን ኮሪያ፣ ኢራን እና ኒካራጉዋ ደግሞ አምባሳደሮቻቸውን ብቻ እንዲልኩ ተጋብዘዋል።
