
15 መስከረም 2022
የግል ጄት በመጠቀም ስደተኞችን ወደ ምዕራብ አውሮፓ ያሻገሩ አምስት ሰዎች ተከሰሱ።
አምስቱ ሰዎች የተከሰሱት በጣሊያን ፍርድ ቤት ነው።
ተጠርጣሪዎቹ ስደተኞቹን ወደ አውሮፓ በግል አውሮፕላን ጭነው ያስገቡት ለሰዎቹ ሐሰተኛ የዲፕሎማት ፓስፖርት ካደሏቸው በኋላ ነው ተብሏል።
ፓስፖርቱ የካሪቢያን ደሴት የሆነችው ሴንት ኪተስ ኤንድ ኔቪሰ እንደሆነ ተመላክቷል።
የግል አውሮፕላኑ እነዚህን ስደተኞች ከቱርክ ከጫናቸው በኋላ በአንድ የአውሮፓ አገር አየር ማረፊያ አራግፈዋቸዋል።
በዚያም ግለሰቦቹ እውነተኛ ማንነታቸውን በመግለጽ የጥገኝነት ጥያቄን አቅርበዋል።
ፖሊስ እንደሚለው እነዚህን ግለሰቦች በግል ጄት ጭኖ አውሮፓ ለማስገባት ተጠርጣሪው ቡድን ከእያንዳንዳቸው 10ሺህ ዩሮ ሳይቀበል አልቀረም።
ድርጊቱን ፈጽመዋል ተብለው ከተጠረጠሩት አምስት ግለሰቦች መሀል ሦስቱ በሮምና በብራስልስ ከተሞች ተይዘዋል።
ሁለቱ አሁንም በፍለጋ ላይ ናቸው።
ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ ጣሊያናዊ ሲሆን ሦስት የግብጽ ዜጎችና አንዲት ቱኒዚያዊት ሴት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፖሊስ ኃላፊ የሆኑት ኮስታንቲኖ ስኩዲየር ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ተጠርጣሪዎቹ የሌላ ግዙፍ ሕገ ወጥ የስደተኛ አሸጋጋሪ ቡድን አባላት እንደሆኑ ግምት በመውሰድ ክስ ተመሥርቶባቸዋል።
ወንጀለኞቹን አድኖ በመያዙ ረገድ ቤልጅየም፣ ጀርመን፣ ኦስትሪያ፣ ፈረንሳይ እና የአሜሪካ የጸጥታና ደኅንነት አካላት እገዛ እንዳደረጉ ተነግሯል።
