News today, social life

ቁጥሮች የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ስለሆነችው ትንሿ ሀገር ኳታር ምን ይላሉ?

የአለም ዋንጫን የምታዘጋጀው ኳታር ስፋት የለንደን ከተማን አታክልም

ኳታር ዶሃ

ከ3 ሚሊየን ገደማ የሚኖርባ ሲሆን፤ የኳታር ዜጎች ከ300 ሺህ አይበልጡም

ኳታር ከ200 ቢሊየን ዶላር ወጪ ያደረገችበት ግዙፉ የዓለም የእግር ኳስ መድረክ የ2022 የዓለም ዋንጫ አዘጋጅታለች።

ውድ የዓለም ዋንጫን ስላዘጋጀቸው ትንሿ ሀገር ኳታር ቁጥሮች ምን ይላሉ?

ኳታር በፈረንጆቹ 1971 ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ ወጥታለች። የአልታኒ ቤተሰብ ከ1825 ጀምሮ ኳታርን እየመራ ነው።

ኳታር 3 ሚሊየን የሚጠጋ ህዝብ ይኖርባታል። ከአጠቃላይ ነዋሪው ግን የሀገሪቱ ዜጋ ከ300 ሺህ አይበልጥም። ከ100 በላይ ሀገራት ዜጎች ይኖሩባታል።

ከ80 በላይ ሀገራት ያለቪዛ መግባት ይችላሉ፤ ይህም ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት አንደኛ ከአለም 8ኛ ደረጃን እንድትይዝ አድርጓታል።

97 በመቶው የተማረ ህዝብ ያለባት ሲሆን፥ የሴቶች እጥረት ግን በስፋት ይስተዋልባታል፤ ከጠቅላላው ህዝብ 24 ነጥብ 7 በመቶው ብቻ ነው ሴት።

ኳታር ወንጀል ከማይፈፀምባቸው ሀገራትም ከ153 ሀገራት 31ኛ ደረጃን በመያዝ ሰላማዊነቷ ተመስክሮላታል።

በየብስ ከሳኡዲ አረቢያ ጋር ብቻ የምትዋሰነው ሀገር ስፋቷ ለንደንን አያክልም፤ የአሜሪካዋን ኒውዮርክ ከተማም 10 በመቶ ብቻ ነው የምትሸፍነው፤ 160 ኪሎ ሜትር ከሰሜን እስከ ደቡብ 80 ኪሎሜትር ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ትረዝማለች።

አራት ማዕዘኗ ሀገር ደሴት ሳይሆኑ ጠባብ ከሆኑ ሀገራት 11ኛ ደረጃ መያዟንም መረጃዎች ያመላክታሉ። በአሳ ሀብቷ የምትታወቀው ዶሃ የተፈጥሮ ጋዝና የነዳጅ ክምችቷ የእድገት ግስጋሴዋን አፋጥኖታል።

ከሩስያና ኢራን በመቀጠል 3ኛዋ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ያለባት ኳታር ለተከታታይ አመታት ፈጣን እድገት አስመዝግባለች።

የሀገሪቱ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ወይም (ጂ ዲ ፒ) 216 ቢሊየን ደርሷል። ከ62 ሺ ዶላር በላይ የደረሰው የነፍስ ወከፍ ገቢም ከአለማችን ባለጠጋ ሀገራት ከፊት አሰልፏታል።

229 ቢሊየን ዶላር ወጪ አድርጋ በ8 ስታዲየሞች ያዘጋጀችውን የአለም ዋንጫ ለማቅረብም ስአታት ቀርተዋል

News today, Politics

ጠ/ሚ ዐቢይ “የወሰን ውዝግብ ያለባቸው አካባቢዎች በህግ አግባብና በምክክር ይፈታሉ” አሉ

መንግስት “ሌብነት” ለመዋጋት በሀገራዊ ኮሚቴ ጥናት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ስለ ሰላም ስምምነቱ “ምን እንደሚመጣ ከወዲሁ መናገር አይቻልም” ብለዋል

የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሄር ፕሬዝዳንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ መስከረም 30፤ 2015 ዓ.ም በሁለቱ ም/ቤቶች መክፈቻ የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫ አሳውቀዋል።

በዚህ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ለመስጠት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ከሀገሪቱ ጠቅላላ ምጣኔ-ሀብት እስከ ፖለቲካ ባህል፤ ከሰላም ስምምነቱ እስከ ደህንነት ስጋቶች ድረስ ከም/ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች መልስና ማብራሪያ ሰጠተዋል።

የሁለት ዓመታትን ጦርነት ይገታል ተብሎ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ስለተደረሰው ሰላም ስምምነትና ስጋት ጥያቄ የተነሰላቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ “ሰላምና ብልጽግናን ለማስቀጠል ሲባል ጦርነትን ማስቆም የግድ ብሏል” ብለዋል።

የኢትዮጵያን ህልውናና አንድነት የሚገዳደር ሲፈጠር ግን “መፋለም” የግድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፤ አሉ ያሏቸውን ሰላም የሚያስከፋቸው ኃይሎችን አሳስበዋል።

ስለ ስምምነቱ ውጤት ሲናገሩም “ምን እንደሚመጣ ከወዲሁ መናገር አይቻልም” ብለዋል። “ሌላውን ተወያይተን ፈር እናስይዘዋለን” በማለትም የስምምነቱ ቀጣይ ድርድሮችና ውይይቶች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።

የምክር ቤቱ አባላት የሚያወዛግቡ አካባቢዎች በፕሪቶሪያው ስምምነት “በህገ-መንግስቱ ምላሽ ይሰጣቸዋል” መባሉ ላይ ጥያቄ አንስተዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ከወልቃይትና ራያ ጀርባ “ሽረባ” አለ ያሉ ሲሆን፤ ለዚህም የመንግስታቸው እጅ እንደሌለበት ተናግረዋል።

በተለይም የወልቃይት ጉዳይ ላይ አተኩረው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ፤ ወልቃይት “የሁለት ህዝቦች ድልድይ ነው” መሆኑን አስምረዋል።

ወዝግቡ በህግ አግባብና በምክክር የሚፈታ ነው ብለዋል። ለወልቃይት “ዲሞክራሲያዊ እድል” መሰጠት አለበት ሲሉም ውዝግቡ በስምምነት እልባት እንደሚያገኝ ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ መንግስታቸው ከስምምነቱ ማግስት ሶስት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ያሳወቁት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ እርዳታ ማቅረብ፣ የወደሙ መሰረተ-ልማቶችን መገንባት እና ተፈናቃዮች መመለስ ላይ መጠመዱን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ስለ ሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት ሲያብራሩ በተለይም ሸኔ ስለተባለው ታጣቂ ቡድን “ፍላጎቱ አይታወቅም” ብለዋል።

መንግስት “ለሰላም ሁሌም በሩ ክፍት ነው” ብለዋል። ህገ-መንግስቱን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገገር በመንግስት በኩል አቋም እንዳለም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በታጣቂው ላይ እየተወሰደ ስላለ እርምጃ ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጡም “ውጤቱ በተጠበቀው ልክ አመርቂ ባይሆንም ስራዎች እየተሰሩ ነው” ሲሉ እየተወሰደ ስላለ ወታደራዊ እርምጃ ፍንጭ ሰጥተዋል።

ህገ-መንግስታዊ መብት ስለሆነው ተንቀሳቅሶ የመስራት መብትም ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ተነስቷል።

ህገ-መንግስታዊ መብት ስለመሆኑ ያልሸሸጉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ሆኖም ለሀገር ሰላም ሲባል መጉላላት እንደ ትልቅ ነገር መታየት እንደሌለበት ገልጸዋል።

ይልቁንም መንገደኞች ለፍተሻ እንዲተባበሩ ጠቁመዋል። “ወጣቶች ብር ተከፍሏቸው አዲስ አበባን ለማሸብት ይሞክራሉ” ያሉም ሲሆን፤ በዚህም የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች እየተያዙ ነው ብለዋል።

ስለ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል አስተያየታቸውን የሰነዘሩም ሲሆን፤ “የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ችግር አለበት” ሲሉም ብቃት መመዘኛ እንዳልሆነ ተናግረዋል።። “ሰፈር ነው የሚታየው” በማለትም “ብሄር” በፖለቲካው መንገሱን ጠቁመዋል። ይህም ባህል እየሆነ ሲሄድ አደገኛ ነው በማለት “በስራ ሳይሆን በጩኸት ለውጥ ይመጣል ብለው የሚፈልጉ ሰዎች የሚያመጡት ነው” ሲሉ አሳስበዋል።

“የሽግግር መንግስት እያሉ የሚጮሁ አሉ፤ ስትጮሁ ትኖራላችውሁ፤ የኢትዮጵያን ክንፍ ነው የምትቆርጡት፤ ጥንቃቄ እናድርግ” ብለዋል።

ስለ ሙስና በሀገሪቱ መንግስት ያነሱት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ “ችግርን እንደ እድል የወሰዱ ሰዎች ቀይ መስመርን ቀይ ምንጣፍ አድርገዋል” በማለት ሌብነት በመንግስት መዋቅር ስር መስደዱን ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።

 ሌብነት ከልምምድ እንደ መብት እየተወሰደ በመሆኑ መንግስት ተወያይቶ ሀገራዊ ኮሚቴ በማቋቋም ጥናት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

“ክሱ ብዙ ነው፤ እጅ የማይጠቆምበት ሰው የለም” በማለትም ህዝቡ ማስረጃ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።

News today, Politics, Technology

ኢራን የጸጥታው ም/ቤት ውሳኔን በመጣስ ለኢትዮጵያ ድሮን መሸጣን አሜሪካ አስታወቀች

ኢራን ሰው አልባ የጦር አውሮፕላን (ድሮን) ለኢትዮጵያ የሸጠችው ከአንድ ዓመት በፊት ነው ተብሏል

ኢራን “ሞሃጀር” የተሰኘውን ድሮን ለኢትዮጵያ መስጠቷን አሜሪካ ገልጻለች

ኢራን የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔን በመጣስ ለኢትዮጵያ ድሮን መሸጧን አሜሪካ አስታወቀች።

የአሜሪካ መንግስት እንዳሳወቀው ኢራን ከአንድ ዓመት በፊት ክረምት ላይ ለኢትዮጵያ ሰው አልባ አውሮፕላን ወይም ድሮን ማስተላለፏን ገልጿል።

ኢራን በፈረንጆቹ 2015 ላይ የጦር መሳሪያ ግብይት እንዳትፈጽም የሚከለክል ማዕቀብ በመንግስታቱ ድርጅት የተወሰነባት ሲሆን፤ ይሄንን ማዕቀብ በመጣስ ለኢትዮጵያ አስተላልፋለች ተብሏል።

2231 የተሰኘው ይህ የተመድ ውሳኔ በኢራን መጣሱን የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቪዳንት ፓቴል መናገራቸውን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ ዘግቧል።

ይህ የተባበሩት መንግስታት ውሳኔ በ2020 ላይ የሚያበቃ ቢሆንም በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ማዕቀቡ እንዲራዘም ጠይቀው ነበር።

ይሁንና ይህ ማዕቀብ እንዲነሳ ያልተወሰነ በመሆኑ ኢራን ውሳኔውን በመጣስ ለኢትዮጵያ አሳልፋ ሰጥታለች ተብሏል፡።

እንደዘገባው ከሆነ ኢትዮጵያ ከኢራን የተረከበችውን ሞሃጀር የተሰኘውን ይሄንን ድሮን ከህወሃት ጋር በሚደረገው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ እንዳዋለችውም ተገልጿል።

ኢራን ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የጦር መሳሪያ ማዕቀቡን በመተላለፍ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ለጀመረችው ጦርነት ድሮን ለሞስኮ ማስተላለፏንም አሜሪካ አስታውቃለች።

ኢራን በምዕራባዊያን የሚቀርቡባትን ክሶች ውድቅ ያደረገች ቢሆንም ከሩሲያ ጋር የሰው አልባ አውሮፕላን እና ሚሳኤል ግዢ ስምምነት መፈጸሟን አምናለች።

ዩክሬን በበኩሏ ኢራን ሻሂድ፣ጄራን እና ሌሎች ስያሜ ያላቸውን ድሮኖች ለሩሲያ በመሸጥ የዩክሬን ዋና ዋና ከተሞች እንዲደበደቡ አድርገዋል በሚል ከቴህራን ጋር ያላትን ግንኙነት እንደምታቋርጥ ዝታለች።

News today, Technology

በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ላይ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር ገለፀ

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው የጉምሩክ ታሪፍ ዝቅተኛ እንደሚሆንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከኤክሳይዝ ታክስና ከሱር ታክስ ነፃ እንደሚደረጉ ተገለፀ

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንትንና አስመጪዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዚህም የታክስ ማሻሻያ ከውጭ የሚገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የኤሌክትሪክ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ የቤት አውቶሞቢሎች እና የእቃ መጫኛ ተሽከርካሪዎች ላይ ዝቅተኛ የጉምሩክ ታሪፍ የሚጣልባቸው መሆኑን ከሚኒስቴሩ ማህበራዊ ገጽ ያኘነው መረጃ ያመለክታል።

እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከኤክሳይዝ ታክስና ከሱር ታክስ ነፃ እንደሚደረጉም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በታክስ ማሻሻያው መሰረት የኤሌክትሪክ የቤት አውቶሞቢሎችን በተመለከተም ሙሉ በሙሉ ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ አውቶሞቢሎች ከጉምሩክ ቀረጥ፣ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ መደረጉን ሚኒስቴሩ ገልጿል

በከፊል ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ የቤት አውቶ ሞቢሎችን በተመለከተም 5 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል።

ሙሉ ለሙሉ ተገጣጥመው ያለቀላቸው የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች ወደ ሀገር ሲገቡ ደግሞ 15 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን፤ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ መወሰኑንም የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኤሌክትሪክ መኪናዎችን በኢትዮጵያ ጎዳናዎች ላይ መታየት ከጀመሩ ዋል አደር ያሉ ሲሆን፤ ግሪን ቴክ አፍሪካ የተባለ ኩባያ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን በኢትዮጵያ መገጣጠም ሊጀምር መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚይ ኢንጅነር ቅደም ተስፋዬ ከወራ በፊት ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አሁን ለይ ከ320 በላይ በኤሌትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት መቻሉን አስታውቀው ነበር።

የተሸከርካሪዎቹ ዋጋ በነዳጅ ከሚሰሩት መኪኖች ጋር ተቀራራቢና እኩል እንደሆነ ያነሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ የጉምሩክ፣ ሱርታክስታና ተጨማሪ እሴት ታክስ ባይኖር ግን ዋጋቸው ከዚህ ይቀንስ እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል።

News today

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ኡሙሩ ወረዳ በታጠቁ ቡድኖች ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ ገለፀ

ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ወደ ኦቦራ ከተማ መፈናቀላቸውንም ኮሚሽኑ አስታውቋል

ኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ኡሙሩ ወረዳ በታጠቁ ቡድኖች በሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለፀ።

ኢሰመኮ ዛሬ ባወጣው መግለጫው በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ስር በሚገኘው ኡሙሩ ወረዳ ከነሐሴ 23 እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በታጣቂ ኃይሎች በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ነዋሪዎች መገደላቸውን፣ መቁሰላቸውን እና መፈናቀላቸውን አስታውቋል።

በዚህም በነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ቀበሌ “ኦነግ ሸኔ” ተብሎ የሚጠራ ታጣቂዎች ኦቦራ ከተማን ለመያዝ ባደረጉት እንቅስቃሴ ሦስት የአማራ ብሔር ተወላጆች መግደላቸውን አሰታውቋል።

ይህንን ተከትሎ ከኡሙሩ ወረዳ፣ ሀሮ አዲስ ዓለም ከተባለ ቀበሌ እና አጎራባች ከሚገኘው የአማራ ክልል፣ ቡሬ ወረዳ የተውጣጡ ታጣቂዎች በኡሙሩ ወረዳ በሚገኙና አገምሳ፣ ጆግ ምግር፣ ታም ኢላሙ፣ ጀቦ ዶባን፣ ጦምቤ ዳነጋበ፣ ጃዋጅ፣ ኛሬ፣ ለገ ሚቻ፣ ሉቁማ ዋሌ በሚባሉ ቀበሌዎች የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ነዋሪዎች ላይ ነሐሴ 24 እና 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ጥቃት ተፈጽሟል ብሏል።

በእነዚህ ሁለት ቀናት በተደረጉ ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፤ ከ70 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን፣ የነዋሪዎች የቤት ንብረቶች እና የቀንድ ከብቶች መዘረፋቸውን ኮሚሽኑ ካነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እና የመንግሥት ኃላፊዎች ለመረዳት መቻሉን አመላክቷል።

ጥቃት ከተፈጸመባቸው ቀበሌዎች መካከል አሁንም ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን እና በጥቃቱ ምክንያትም ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ተፈናቅለው በኦቦራ ከተማ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በተጨማሪም በጥቃቶቹ ምክንያት የተፈጠረው የደኅንነት ስጋት ያልተቀረፈ መሆኑን እና በዞኑ ውስጥ ካሉት ወረዳዎች መካከል በጃርደጋ ጃርቴ፣ ኪረሙ እና በአቤ ዶንጎሮ ወረዳዎች ተመሳሳይ ጥቃቶች ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ስጋቶች መኖራቸውን ኮሚሽኑ ከነዋሪዎች ያሰባሰባቸው መረጃዎች ያሳያሉ ብሏል፡፡

በሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃቱ የተፈፀመው በአካባቢው ተሰማርቶ የነበረ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሌላ አካባቢ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ መሆኑን ኮሚሽኑ በመግለጫው አክሏል።

ኮሚሽኑ ጥቃት በተፈጸመባቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እንዲሰማሩ እና ሰላምና ደኅንነትን በማረጋገጥ ነዋሪዎችን ወደ ተረጋጋ ሕይወት የመመለስና ተገቢውን ምርመራ አድርጎ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራ እንዲሠራ አሳስቧል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ኮሚሽኑ ክትትል ማድረጉን የሚቀጥል መሆኑንና በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመው አሳዛኝ ጥቃት ያሳሰበው መሆኑን ገልጸው፤ በማንኛውም ጊዜ የፀጥታ ስጋት ካለባቸው አካባቢዎች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሌላ ቦታ በሚዘዋወሩበት ወቅት የነዋሪዎች በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት እና የንብረት መብቶች ለአደጋ እንዳይጋለጡ ተገቢ የሆኑ ጥንቃቄዎች ሊደረጉ እንደሚገባ በድጋሚ አስታውሰዋል።