
ከ 6 ሰአት በፊት
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር የኡጋንዳ ጉብኝትን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ማንም ትዕዛዝ አይሰጠንም ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።
አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝታቸው ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 28/2014 ዓ.ም. ከኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ጋር ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አምባሳደሯ ከዋሽንግተን ዲሲ መመሪያዎችን ይዘው ይመጡ እንደሆነ የተጠየቁት ሙሴቬኒ፤ “ማንም ትዕዛዝ አይሰጠንም” ሲሉ መልሰዋል።
ሙሴቬኒ አገራቸው ኡጋንዳ ከምዕራባውያን የሚላከውን እርዳታ በመልካም ጎኑ እንደምትመለከተው ጠቅሰው፤ አገራቸው ያለ እርዳታ መኖር እንደምትችልም ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ኡጋንዳ በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ የያዘችውን አቋም ለማስቀየር የተደረገ ጥረት እንደሌለ ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ወረራ እንድታቆም ያወጣውን ምክር ሃሳብ በድምጸ ታዕቅቦ ካለፉት 16 የአፍሪካ አገራት መካከል ኡጋንዳ አንዷ መሆኗ ይታወቃል።
አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪን ፊልድ ወደ ካምፓል የሚያመሩት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኡጋንዳ ጉብኝት ካደረጉ ከቀናት በኋላ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በቅርቡ ኡጋንዳ እና ኢትዮጵያን ጨምሮ በአራት የአፍሪካ አገራት ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ሙሴቬኒ፤ “ጥሩ ጓደኛ” ሲሉ የገለጿቸው አምባሳደር ቶማስ-ግሪንፊልድን ሁሌም ወደ ኡጋንዳ እንዲመጡ በራችን ከፍት ነው ካሉ በኋላ፤ አስተዳደራቸው ለምዕራባውያን ጫና እንደማይበረከክ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ አቋማቸው ምን እንደሆነ ሲጠየቁ፤ ጦርነቱን ከ1962ቱ የኩባ ሚሳኤል ቀውስ ጋር አነጻጸረውታል።
ሙሴቪኒ ዛሬ ላይ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በሩሲያ ዙሪያ መገኘትን ሶቪየት ሕብረት አሜሪካ አፍንጫ ስር ኩባ ውስጥ ሚሳኤል ከመትከሏ ጋር አነጻጽረውታል።
የኩባ ሚሳኤል ቀውስ ተብሎ የሚታወቀው ክስተት የወቅቱ የዓለማችን ኃያላንን ወደ ኒውክሌር ጦርነት እንዲገቡ ከጫፍ አድርሶ ነበር።
በወቅቱ ሶቪየት ሕብርት የኩባን ደኅንነት ከአሜሪካ ጥቃት ለመጠበቅ በሚል፣ ኩባ ውስጥ የአሜሪካ ከተሞችን መምታት በሚያሰችሉ ስፍራዎች ላይ የኒውክሌር አረሮችን ማስወንጨፍ የሚችሉ ሚሳኤሎችን ተክላ ነበር።
ሙሴቬኒ ይህ ክስተት የአሜሪካንን የደኅንነት ስጋት ውስጥ ከትቶ እንደነበረ ተናግረው፤ በወቅቱ አገራቸው ለአሜሪካ ድጋፏን መሽጠቷን አስታውሰዋል።
ሙሴቬኒ ዛሬም ተመሳሳይ መርኅ ማረመድ አለብን ብለዋል።
ሙሴቬኒ ኔቶ በሩሲያ ዙሪያ መክተሙ፤ የሩሲያን እርምጃ እንዲገነዘቡ ያደርግዎታል ወይ ተብለው ሲጠይቁ፤ “በትክክል” ሲሉ መልሰዋል።
“ታሪክ የምትሉትን፤ እኔ ወቅታዊ ጉዳይ እለዋለሁ” ብለዋል ሙሴቬኒ።
