2 ነሐሴ 2022, 11:17 EAT
አፍጋኒስታን ውስጥ በአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት የተገደለው አይማን አል-ዛዋህሪ የአል ቃኢዳ ርዕዮተ ዓለም ዋና ጠንሳሽ ተብሎ ይጠራ ነበር።
ግብጻዊ ነው። የግብጽን እስላማዊ ጂሃድ ታጣቂ ቡድን ለመመስረትም ድጋፍ በማድረግ ይታወቃል።
አል-ዛዋህሪ የዓይን ቀዶ ሕክምና ባለሙያ ነው። እአአ ግንቦት 2011 የአሜሪካ ጦር ኦሳማ ቢን ላደን መገደሉን ተከትሎ የአል ቃኢዳ መሪ ሆነ።
ከዚያ በፊት አል-ዛዋህሪ የቢን ላደን ቀኝ እጅ እንደሆነ ይቆጠር ነበር። አንዳንድ ባለሙያዎች መስከረም 1/2001 በዩናይትድ ስቴትስ ከደረሰው ጥቃት ጀርባ የሚገኝ “ዋና ሰው” እንደሆነ ይታመናል።
የአሜሪካ መንግስት በአውሮፓውያኑ 2001 “በጣም የሚፈለጉ አሸባሪዎች” ብሎ ከዘረዘራቸው 22 ሰዎች አንዱ ነው። በቢንላደን ብቻ ተቀድሞ አል-ዛዋህሪ ቁጥር ሁለት ላይ ተቀምጧል። አሜሪካ ያለበትን ለጠቆመ 25 ሚሊየን ዶላር እሸልማለሁ ብላ ነበር።
ከጥቃቶቹ በኋላ በነበሩት ዓመታት አል-ዛዋህሪ የአልቃኢዳ ዋነኛው ቃል አቀባይ ሆኖ ብቅ አለ። በ2007 ብቻ 16 ቪዲዮዎችን እና የድምጽ መልዕክቶችን አስተላልፏል። ይህ ከቢንላደን በአራት እጥፍ የሚበልጥ ቁጥር ነው።
ትኩረቱንም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሙስሊሞችን አክራሪ ለማድረግ እና ለመመልመል መሞከር ነበር።
ከቀናት በፊት በካቡል በተፈጸመ ጥቃት ነው አይማን አል-ዛዋህሪ የተገደለው። አሜሪካ ግለሰቡን ለማጥቃት ስትሞክር ግን የመጀመሪያዋ አልነበረም።
ጥር 2006 ፓኪስታን ከአፍጋኒስታን ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አካባቢ አሜሪካ የሚሳኤል ጥቃት ዒላማዋ አድርጋው ነበር።
ጥቃቱ አራት የአልቃይዳ አባላትን ገድሏል። አል-ዛዋህሪ በሕይወት ተርፎ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ታየ። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽም ሆኑ “በምድር ላይ ያሉ ኃያላን” ሞቱን “በአንድ ሰከንድ” ሊያቀርቡት እንደማይችሉ አስጠነቀቀ።
ከተከበረ ቤተሰብ የተገኘው ዶክተር
አይማን አል-ዛዋህሪ በአውሮፓውያኑ ሰኔ 19 ቀን 1951 በግብጽ ርዕሰ መዲና ካይሮ ተወለደ። የተገኘው ከተከበሩ ሐኪሞች እና ምሁራን ቤተሰብ ነው።
አያቱ ራቢያ አል-ዛዋህሪ በመካከለኛው ምስራቅ የሱኒ እስላማዊ ትምህርት ማዕከል በሆነው የአል-አዝሃር ኢማም ነበሩ። አንዱ ከአጎቱ የአረብ ሊግ የመጀመሪያው ዋና ጸሐፊ ሆነው አገልግለዋል።
አይማን አል-ዛዋህሪ በትምህርት ቤት እያለ በፖለቲካዊ እስልምና ውስጥ ተሳትፏል። ህገ-ወጥ በሆነው የሙስሊም ወንድማማቾች አባል በመሆኑ በ15 ዓመቱ ለእስር በቅቶ ነበር። ይህ የግብጽ ትልቁ እስላማዊ ድርጅት ነው።
የፖለቲካ ዝንባሌው በካይሮ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት ሕክምናን ከመማር አላገደውም። በ1974 ተመረቀ። ከአራት ዓመት በኋላ ደግሞ በቀዶ ሕክምና ሁለተኛ ዲግሪውን አግኝቷል።
በ1995 ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አባቱ መሐመድ በዚሁ ትምህርት ቤት የፋርማኮሎጂ መምህር ነበሩ።
አክራሪው ወጣት
አይማን አል-ዛዋህሪ መጀመሪያ የቤተሰቡን ዱካ ተከተለ። በካይሮ አካባቢ የህክምና ክሊኒክ ከፈተ። ብዙም አልገፋበትም። በኋላም የግብጽን መንግሥት ለመጣል በሚጥሩ አክራሪ እስላማዊ ቡድኖች ተማረከ።
በአውሮፓውያኑ 1973 የግብጽ እስላማዊ ጂሃድ ተመሠረተ። አል-ዛዋህሪም ተቀላቀለ።
የቡድኑ የወታደር ልብስ ለብሰው ፕሬዝዳንት አንዋር ሳዳትን በካይሮ ወታደራዊ ትርኢት ላይ ገደሏቸው። ይህን ተከትሎም እአአ በ1981 ላይ ከበርካታ ተጠርጣሪ የቡድኑ አባላት ጋር በቁጥጥር ስር ዋሉ። ሳዳት ከእስራኤል ጋር የሠላም ስምምነት በመፈራረማቸው በቡድኑ ዘንድ ቁጣ ተቀሰቀሰ። ቀደም ሲልም የጸጥታ ሃይሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የፕሬዝዳንቱን ተቺዎች ማሰራቸው ቂም ፈጥሮ ነበር።
በጅምላ ችሎቱ ወቅት አል-ዛዋህሪ የተከሳሾቹ መሪ ሆኖ ቀርበ። “እኛ በዲናችን የምናምን ሙስሊሞች ነን። እስላማዊ መንግሥት እና እስላማዊ ማህበረሰብ ለመመስረት እየጣርን ነው” ሲል ለፍርድ ቤቱ ሲናገር ተቀርጿል።
በሳዳት ግድያ ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌለው ተገለጸ። ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ በመያዝ ተከሶ ግን ሦስት ዓመት እስራት ተላለፈበት።
እንደ እስላማዊ እስረኞች ገለጻ ከሆነ አል-ዛዋህሪ በግብጽ እስር ቤት በባለስልጣናት አዘውትሮ ይሰቃይና ይደበደብ ነበር። ይህም አክራሪ እንዲሆን አድርጎታል ተብሏል።
በ1985 ከእስር የተፈታው አይማን አል-ዛዋህሪወደ ሳዑዲ አረቢያ አቀና።
ሳዑዲ ብዙም አልቆየም። ወደ ፓኪስታኗ ፔሻዋር አመራ። ቀጥሎ ወደ ጎረቤት አፍጋኒስታን አቀና። በሶቪየት ወረራ ወቅት በሐኪምነት ከመስራት ጎን ለጎን የግብጽ እስላማዊ ጂሃዳዊ አንጃን አቋቋመ።
የግብጽ እስላማዊ ጂሃድ በ1993 እንደገና ሲያንሰራራ አል-ዛዋህሪ መሪነቱን ተረከበ። ቡድኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አጢፍ ሲድቂን ጨምሮ በግብጽ ሚኒስትሮች ላይ ተከታታይ ጥቃት ሰነዘረ። እሱም የጥቃቶቹ ቁልፍ ሰው ነበር።
በ1990ዎቹ አጋማሽ ቡድኑ መንግሥትን ለመጣል እና እስላማዊ መንግሥት ለመመስረት ዘመቻ አካሄደ። ይህም ከ1 ሺህ 200 በላይ ግብጻውያንን ለህልፈት ዳርጓል።
እአአ በ1997 የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዲፓርትመንት የቫንጋርድስ ኦፍ ኮንክሰስ ቡድን መሪ ነው ሲል ሰይሞታል። ይህ የእስልምና ጂሃድ ቡድን በዛው ዓመት በሉክሶር ከተካሄደው የውጭ ቱሪስቶች እልቂት ጀርባ ነበር።
ከሁለት ዓመት በኋላ በሌለበት በግብጽ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የሞት ፍርድ ተላልፎበታል። በቡድኑ ጦሩ ላይ ባደረሰው በርካታ ጥቃቶች ሚና ነው ውሳኔው የተላለፈበት።
ምዕራባውያን ዒላማዎች
አይማን አል-ዛዋህሪ እአአ በ1990ዎቹ ለሐይማኖታዊ እና የገንዘብ ድጋፍ ፍለጋ በዓለም ዙሪያ ተዘዋውሯል ተብሎ ይታሰባል።
ሶቪዬት አፍጋኒስታንን ለቃ ከወጣች በኋላ በነበሩት ዓመታት በቡልጋሪያ፣ ዴንማርክ እና ስዊዘርላንድ ይኖር ነበር። አንዳንዴ ሐሰተኛ ፓስፖርት በመጠቀም ጭምር ወደ ባልካን፣ ኦስትሪያ፣ የመን፣ ኢራቅ፣ ኢራን እና ፊሊፒንስ ተጉዞ እንደነበር ይገመታል።
በታህሳስ 1996 ደግሞ ቺቺኒያ ውስጥ ህጋዊ ቪዛ ሳይኖረው ተይዞ ለስድስት ወራት ያህል በሩሲያ እስር ቤት እንደቆየ ይነገራል።
በአይማን አል-ዛዋህሪ ተጽፏል በተባለው ጽሑፍ መሠረት የሩሲያ ባለስልጣናት በኮምፒዩተሩ ላይ የነበሩ አረብኛ ፅሁፎችን መተርጎም ባለመቻላቸው ማንነቱን በሚስጥር መያዝ ችሏል።
እአአ በ 1997 አል-ዛዋህሪ ኦሳማ ቢን ላደን ወደከተመባት አፍጋኒስታኗ ጃላላባድ ከተማ እንዳቀና ይታመናል።
ከአንድ ዓመት በኋላ የግብጽ እስላማዊ ጂሃድ የቢን ላደኑን አልቃይዳን ጨምሮ ሌሎች አምስት አክራሪ እስላማዊ ታጣቂ ቡድኖችን በመቀላቀል በአይሁዶች እና በመስቀል ጦረኞች ላይ የዓለም እስላማዊ ጂሃድን መሠረተ።
የቡድኑ የመጀመሪያ አዋጅ የአሜሪካ ዜጎችን መገደል የሚፈቅደውን ፈትዋ ወይም ሃይማኖታዊ ድንጋጌን ያካትታል። ከስድስት ወራት በኋላ በኬንያ እና በታንዛንያ የሚገኙት የአሜሪካ ኤምባሲዎች በተመሳሳይ ወቅት ጥቃት ተፈጽሞባቸው 223 ሰዎች ሞቱ።
ከሴራው ጀርባ ቢንላደን እና አልቃኢዳ መኖራቸውን ለማረጋገጥ ከተወሰዱት ነገሮች አንዱ የአል-ዛዋህሪ የሳተላይት የስልክ ንግግር ነበር።
ጥቃቱ ከተፈጸመ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ በአፍጋኒስታን የሚገኘውን የቡድኑን ማሰልጠኛ ካምፖች በቦምብ ደበደበች። በማግስቱ አይማን አል-ዛዋህሪ ለአንድ የፓኪስታን ጋዜጠኛ ደውሎ “የቦምብ ፍንዳታው፣ ዛቻው እና ጥቃቱ አያስፈራንም። ጦርነቱ ገና አሁን መጀመሩን ለአሜሪካ ንገራት” ብሎ ነግሮታል።
ከቢንላደን ሞት በኋላ በነበሩት ዓመታት የአሜሪካ የአየር ጥቃት የአል-ዛዋህሪ ምክትሎች ለመግደል አስችሏታል። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረ አቅሙን አዳክሞታል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ አል-ዛዋህሪ ሩቅ እና የተገነጠለ ሰው ሆነ ነበር። መልዕክቶችንም አልፎ አልፎ ብቻ ነበር የሚሰጠው።
አሜሪካ ባለፈው ዓመት ከአፍጋኒስታን የወጣችበት መንገድ በግርግር እና በጥድፊያ የተሞላ ነበር። እስላማዊ መንግሥት ያሉ አዳዲስ ቡድኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጽዕኖ እያሳደሩ በመሆናቸው አል-ዛዋህሪ ብዙም ስልጣን አሜሪካ መሞቱን እንደ ድል ታበስራለች።
አልቃኢዳ አዲስ መሪ ይፋ እንደሚደረግ ምንም ጥርጥር የለውም። አዲሱ መሪ ግን አይማን አል-ዛዋህሪ ያነሰ ተጽዕኖ ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል።