
የአውስትራሊያው አየር መንገድ ካንታስ የጉልበት ሠራተኞች እጥረት ስላጋጠመው የአየር መንገዱ ከፍተኛ አመራሮች ሻንጣ በመጫን እና በማውረድ እንዲያግዙት ጠየቀ።
የአየር መንገዱን የዕለት ከዕለት የመንገደኞች ማስተናገድ ሥራውን የሚካታተለው ክፍል እንደገለጸው፣ ሲድኒ እና ሜልበርን ውስጥ በሚገኙ አየር ማረፊያዎች ቢያንስ 100 በጎ ፈቃደኛ የጉልበት ሠራተኞችን እንደሚፈልግ አስታውቋል።
ካንታስ የሚፈልጋቸው የጉልበት ሠራተኞች ሻንጣዎችን ከአውሮፕላኖች ላይ በማውረድና በመጫን እንዲሁም ሻንጣ የሚጫንባቸው ተሽከርካሪዎችን በአየር ማረፊያዎች ውስጥ የሚያንቀሳቅሱ ሾፌሮችን ነው።
በኮሮናቫይረስ ምክንያት አገራት ድንበሮቻቸውን ለአየር በረራዎች ዝግ አድርገው ከቆዩ በኋላ አሁን መክፈት በመጀመራቸው፣ ካንታስን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ያሉ አየር መንገዶች የተለያዩ ፈተናዎች እየገጠሟቸው ነው።
“ጉንፋን እና ኮቪድ በከፍተኛ ሁኔታ መሰራጨቱ እና በገበያው ላይ ሠራተኞችን ለማግኘት ያለው ፈተና አየር መንገዶች ሥራቸውን በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዳያከናውኑ እንቅፋት ፈጥሯል” ሲሉ የካንታስ ባለሥልጣን የሆኑት ኮሊን ሁግስ ለቢቢሲ በኢሜይል ገልጸዋል።
“ያለው አማራጭ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ሙሉ ጊዜያቸውን ወደሚሰሩ ሰዎች ፊትን ማዞር ነው” ሲሉም ሁግስ አክለዋል።
በዚህም ሳቢያ የካንታስ አየር መንገድ ሥራ አመራሮች ለቀጣይ ሦስት ወራት በፈረቃ፣ በቀን ለስድስት ወይም ለአራት ሰዓታት፣ በሳምንት ለሦስት ወይም ለአምስት ቀናት ሻንጣ የመጫን እና የማውረድ ሥራን እንዲያከናውኑ ተጠይቀዋል።
ካንታስ ባሰራጨው መልዕክት ላይ ለሻንጣ ጫኝነት እና አውራጅነት የሚያመለክቱ ኃላፊዎች ብቻቸውን አስከ 32 ኪሎ ግራም የሚመዝን ክብደት የማንሳት አቅም ሊኖራቸው ይገባል።
“አስካሁን ባለው ሥራችን የደንበኞቻችንን ፍላጎት እና የሚጠበቀውን ደረጃ ማሟላት እንዳላቻልን ግልጽ ነው፣ ስለዚህ ሥራችንን ለማሻሻል ሁሉንም ነገሮች ማድረግ ይጠበቅብናል” ሲሉ የካንታስ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አየር መንገዱ ከዚህም በፊት ከፍተኛ የመንገደኞች ቁጥር ለማስተናገድ በተገደደበት ጊዜ 200 የሚደርሱ የቢሮ ውስጥ ሠራተኞቹን በተመሳሳይ ሥራ ላይ እንዲያግዙት ማድረጉን አመልክቷል።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት አገራት የአየር ክልሎቻቸውን መዝጋታቸውን ተከትሎ ከባድ ቀውስ ከገጠማቸው አየር መንገዶች መካከል ካንታስ አንዱ ነው።
በዚህም ሳቢያ በመላው ዓለም ያሉ አየር መንገዶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቻቸውን መቀነሳቸው ይታወሳል።
አገራት የወረርሽኙን መስፋፋት ለመግታት ወስደዋቸው የነበሩትን ጥብቅ እርምጃዎችን በአሁኑ ወቅት ማላላት በመጀመራቸው ካንታስ እና ሌሎች አየር መንገዶች ሥራቸውን በቀደመው መልኩ ለማካሄድ ፈተና ገጥሟቸዋል።
