News today, Politics

ብሊንከን ሩሲያ በአፍሪካ ያላትን ተፅዕኖ ለመመከት ያለመ ጉብኝታቸውን ጀመሩ

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሩሲያ በአፍሪካ ያላትን ተፅዕኖ ለማሳደግ የምታደርገውን የዲፕሎማሲ ጥረት ለመመከት ያለመ ጉብኝት ጀመሩ።

ብሊንከን በዚህ ጉብኝታቸው ወደ ሦስት የአፍሪካ አገራት እንደሚጓዙ ይጠበቃል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከደቡብ አፍሪካ በኋላ ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ሩዋንዳ ይሄዳሉ ተብሏል።

የብሊንከን የመጀመሪያ መዳረሻ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ በዩክሬኑ ጦርነት ሞስኮን ለማውገዝ የምዕራባውያንን ጥሪዎች ሳትቀበል ገለልተኛ ሆና ቆይታለች።

ከሁለት ሳምንታት በፊት የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ስድስት ቀናትን በፈጀ ጉብኝት አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ተለያዩ አገራት ተጉዘው ነበር።

ላቭሮቭ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በግብጽ ጀምረው ቀጥሎም ወደ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ዩጋንዳ እና ኢትዮጵያ ተጉዘው ከባለስልጣናት ጋር ተገናኝተዋል።

በቆይታቸውም በተለይም በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት በአፍሪካ በተከሰተው የስንዴ አቅርቦት እጥረት ላይ ትኩረት ሰጥተው ንግግሮችን አካሂደው ለምግብ እጥረቱ ተጠያቂዎቹ ምዕራባዊያን አገራት ናቸው ሲሉም ተደምጠዋል።

“ምዕራባውያን አገራት የበላይነታቸውን በሌሎች ላይ ለመጫን እየሞከሩ ነው” ሲሉም ከሰዋል። እንዲሁም ሞስኮ የዓለምን የምግብ ቀውስ አስከትላለች የሚለውን ወቀሳ አጣጥለውታል።