News today, Politics

የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር አንቶኒ ብሊንከን የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ጀመሩ


ብሊንከን በአፍሪካ ጉብኝታቸው ከፕሪቶሪያ በተጨማሪ ኬንሻሳ እና ኪጋሊን ይጎበኛሉ ተብሏል
የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር አንቶኒ ብሊንከን የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ጀመሩ።
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት መጀመራን ተከትሎ በሩሲያ ላይ ጫና ለመፍጠር ከወራት በፊት በመንግስታቱ ድርጅት በተጠራ ስብሰባ ላይ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ድምጸ ተዓቅቦ ማድረጋቸው አሜሪካንን ጨምሮ ምዕራባዊያንን አስቆጥቷል።
“ሉዓላዊነትን እና ግዛታዊ አንድነትን ማክበር ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋትና ልማት አስፈላጊ ነው” – ብሊንከን 
ከዚህ ጊዜ ጀምሮም በተለያዩ ጊዜያት የአሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ አፍሪካ በመጓዝ ጫና በማድረግ ላይ ናቸው።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ሩሲያን ከተቀረው ዓለም የመነጠል ስራውን ለማጠናከር የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ጀምረዋል።
ብሊንከን ከሰዓታት በፊት ደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ የደረሱ ሲሆን ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ስሪል ራሞፎሳ ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
ብሊንከን ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪም ሩዋንዳን እና ዲሞክራቲክ ኮንጎን እንደሚጎበኙ አስታውቀዋል።
ብሊንከን በአፍሪካ ቆይታቸው በምግብ ደህንነት ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ ንግድ እና ጤና ጉዳዮች ዙሪያ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር እንደሚመክሩ ተናግረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ከነዚህ ጉዳዮች በተጨማሪ በግጭት ውስጥ ያሉት ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ ግንኙነታቸው እንዲሻሻል እንደሚሰሩም ተገልጿል።
እንዲሁም አንቶኒ ብሊንከን በኪጋሊ ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ጋር በስህተት ስለታሰሩት የሆቴል ሩዋንዳ ፊልም ሰሪ ፖል ሩሴሳባጊና ጉዳይ እንደሚወያዩም ይጠበቃል ተብሏል።
አንቶኒ ብሊንከንና ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተወያዩ 
የአንቶኒ ብሊንከን የአፍሪካ ጉብኝት የሩሲያው አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ሶስት የአፍሪካ ሀገራትን ጎብኝተው ከተመለሱ በኋላ መሆኑ የጉዟቸው አላማ የሩሲያን ተጽዕኖ ከአፍሪካ ለመነጠል ያለመ እንደሆነ ሌሎች ዘገባዎች እየወጡ ይገኛል።
አንቶኒ ብሊንከን የአሁኑ የአፍሪካ ጉብኝት ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ባሳለፍነው ህዳር ላይ ናይጀሪያ፣ ሴኔጋል እና ኬንያን ጎብኝተው መመለሳቸው ይታወሳል።