News today, Politics, social life

በእስራኤል ጥቃት አንድ የታጣቂ ቡድን መሪን ጨምሮ አስር ሰዎች ተገደሉ


እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት አንድ የፍልስጤም ታጣቂዎች ቡድን መሪን እና አንዲት ህጻንን ጨምሮ 11 ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርቶች አመለከቱ።

ይህን የእስራኤል ጥቃት ተከትሎ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ሮኬቶች ከጋዛ ወደ እስራኤል የተተኮሱ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በአካባቢው ከባድ ውጥረት ነግሷል።

ይህንንም ተከትሎ እስራኤል በወረራ በያዘችው የዌስት ባንክ አካባቢ ባደረገችው አሰሳ 19 የኢስላሚክ ጂሃድ ቡድን አባላት ናቸው የተባሉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሏ ተገልጿል።

በእስራኤል ጥቃት ከተገደሉት 11 ሰዎች መካከል ታይሰር ጃባሪ የተባለ የታጣቂዎች መሪ ይገኝበታል።

የአየር ጥቃቱ ግለሰቡ የሚመራው የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ የተባለው ቡድን “ጥቃት ሊሰነዝር” መሆኑን ተከትሎ የተወሰደ እርምጃ ነው ስትል እስራኤል ምክንያቷን አሳውቃለች።

ከተገደሉት መካከል የአምስት ዓመት ታዳጊ የምትገኝበት ሲሆን፣ ሌሎች በርካቶች ደግሞ የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው የአካባቢው የጤና ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ የተባለው ቡድን ለእሰራኤል ጥቃት “የመጀመሪያ ምልሽ” ባለው አጸፋ ከ100 በላይ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ሌሊቱን ተኩሷል።

ከተተኮሱት ሮኬቶች አብዛኞቹ በእስራኤል የሚሳኤል መከላከያ አማካይነት መክሰማቸው የተነገረ ሲሆን፣ በበርካታ የእስራኤል ከተሞች ውስጥ ሌሊቱን በሙሉ የጥቃት ማስጠንቀቂያ ደውሎች ሲሰሙ አድረዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር እስከ ቅዳሜ ንጋት ድረስ የዘለቁ የሮኬት ጥቃቶችን ጋዛ ውስጥ በሚገኙ በርካታ የታጣቂዎቹ ይዞታዎች ላይ ሲፈጽም ማደሩን ኣሰውቋል።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ተመሳሳይ ግጭት ተከስቶ ከ200 በላይ ፍልስጤማዊያን እና በርካታ እስራኤላውያን ከተገደሉ በኋላ በግብፅ አደራዳሪነት የተኩስ አቁም መደረሱ ይታወሳል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ያይር ላፒድ ሠራዊታቸው ለአገራቸው ስጋት በሆኑ ኢላማዎች ላይ ፈጣን ፀረ ሽብር ጥቃት መፈጸሙን የገለጹ ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ደግሞ ግጭቱ የተራዘመ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን አመልክተዋል።

ጋዛ ውስጥ በእስላማዊ ቡድን ኢላማዎች ላይ ነው የተፈጸመው በተባለው ጥቃት “15 የሚሆኑ ታጣቂዎች” መገደላቸውን የእስራኤል ሠራዊት ቃል አቀባይ መናገራቸው ተዘግቧል።

የጋዛ የጤና ባለሥልጣንት ግን ታይሲር ጃባሪን ጨምሮ አራት የእስላማዊ ቡድኑ ታጣቂዎች በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን አረጋግጠዋል።

የእስራኤል የመከላከያ ኃይል ታይሲር ጃባሪ የፍልስጥኤም እስላማዊ ጂሃድ ቡድን “ከፍተኛ መሪ” መሆኑን እና “በርካታ የሽብር ጥቃቶችን” በእስራኤላውያን ሰላማዊ ሰዎች ላይ ፈጽሟል ሲል ይከሰዋል።

የጋዛ ባለሥልጣናት እንዳሳወቁት በጥቃቱ ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ 79 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው መናገራቸውን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ዘግቧል።

የፍልስጥኤም እስላማዊ ጂሃድ ቡድን ዋና ፀሐፊ ዚያድ አል-ናኻላ ወደ ኢራን በጉዞ ላይ ሳሉ “ለተፈጸመው ጥቃት በሙሉ ኃይላችን ምላሽ እንሰጣለን፣ በአሸናፊነት የምንወጣበት ጦርነት ይሆናል። የማይነካ ቦታ አይኖርም፣ ቴል አቪቭ በሮኬቶቻችን ጥቃት ስር ትሆናለች” ማለታቸው ተዘግቧል።

የጋዛ ሰርጥን የሚያስተዳድረው ሐማስ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች ዝም እንደማይሉና በሚካሄደው ዘመቻ ውስጥ በአንድነት እንደሚቆሙ ገልጿል።