
ከ 5 ሰአት በፊት
የአሜሪካ ጦር በሶማሊያ ማዕከላዊ ሒራን ክልል በአልሻባብ ተዋጊዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙን የሶማሊያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።
መገናኛ ብዙኃኑ እንዳለው ጥቃቱ የተፈፀመው የሶማሊያ መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ነው።
የአየር ድብደባ ስለመፈፀሙ ግን የአሜሪካ እና አፍሪካ ወታደራዊ ዕዝ አስተያየት አልሰጠም።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት በሰኔ እና በሐምሌ ወር በተፈፀሙ ሁለት የአየር ድብደባዎች ሰባት የጂሃዲስት ቡድኑ ተዋጊዎች መገደላቸውን መናገራቸው ይታወሳል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ አልሻባብ በመንግሥት ኢላማዎች ላይ የሚፈጽመው ጥቃት የጨመረ ሲሆን በቅርቡም ድንበር በመሻገር በኢትዮጵያ ደንገተኛ ጥቃት ፈጽሟል።
አሜሪካ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት በአል ሻባብ ቡድን ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በሰው አልባ አውሮፕላኖች ስትፈጽም ቆይታለች።
በተለይም የቡድኑን አመራሮች ኢላማ በማድረግ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ከፍተኛ መሪዎቹን ጨምሮ በርካታ የቡድኑ አባላትን መግደሏ መዘገቡ ይታወሳል።
ሐምሌ 13/2014 ዓ.ም እስላማዊ ታጣቂዎቹ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንባቸው የድንበር ከተሞች የከፈቱትን ጥቃት ተከትሎ ከባድ ውጊያ ተካሂዶ ነበር።
ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት አለው የሚባለው አልሻባብ ጥቃቱን የፈፀመው ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንበት ግዛት በኩል በሚገኙት ዬድ እና አቶ ላይ ነው።
ከኢትዮጵያ ጋር በሚዋሰኑት የሶማሊያ ድንበር አካባቢዎች ነበሩ በተባሉ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት ጋር በተካሄደው በዚህ ከባድ ውጊያም በሁለቱም ወገን ጉዳት መድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ዑመርም እስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ የከፈተውን ጥቃት የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች መክተው መመለሳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ድንበር ተሻግረው ጥቃት ከሰነዘሩት የአልሻባብ አባላት መካከል ከ800 በላይ የሚሆኑ መገደላቸውንና በርካቶች መማረካቸውን ገልጿል።
ቀደም ሲልም የኢትዮጵያ ሠራዊት በቡድኑ ላይ ወሰዳቸው ወታደራዊ እርምጃዎች በአሜሪካ በጥብቅ ሲፈለግ የነበረ ግለሰብን ጨምሮ ሦስት ከፍተኛ የአልሻባብ ከፍተኛ አመራሮችን መግደሉን አሳውቋል።
በተያያዘ ዜና የአልሻባብ ታጣቂ ቡድን የቀድሞ መሪ የሆነው ሙክታር ሮቦው አዲስ በተቋቋመው ካቢኔ ውስጥ የሶማሊያ የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር በመሆን ባለፈው ሳምንት ተሹመዋል።
የእርሳቸው ሹመትም የአል ሸባብን ጽንፈኛ ርዕዮተ ዓለም ለመመከት የተደረገ ሙከራ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል።
