News today, social life

ሲም ካርድ ያለው ሁሉ ገንዘብ መበደር የሚችልበትን ዕድል ለመፍጠር ያቀደው ቴሌብር

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ

ከአስራ አራት ወራት በፊት ወደ አገልግሎት የገባው ቴሌብር የተሰኘው የኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ገንዘብ ሥርዓት ባለፈው ሳምንት አርብ ከቁጠባ እና ብድር ጋር የተያያዙ አዳዲስ አገልግሎቶችን መስጠት ጀምሯል።

ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ አዳዲሶቹ አገልግሎቶች በፋይናንስ ሥርዓት ያልተሸፈነውን 60 በመቶ የሚሆን የኅብተረሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

የነዳጅ ድጎማ እና የግብር ክፍያን ጨምሮ ባለፉት 14 ወራት ገንዘብ ለመላላክ፣ የግብይትና የአገልግሎት ክፍያን ለመፈጸም እንዲሁም ከውጭ አገራት ገንዘብ ለመቀበል ሲውል የነበረው ቴሌብር አሁን ደግሞ  ‘መላ’፣ ‘እንደኪሴ’ እና ‘ሰንዱቅ’ የተሰኙ አገልግሎቶችን ይፋ አድርጓል።

ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌብር ደንበኞች ገንዘብ እንዲቆጥቡ፣ ሲያስፈልጋቸው እንዲበደሩ የሚረዱት አዳዲሶቹን አገልግሎቶች ለማስጀመር አስራ አራት ወራት በላይ ዘግይቷል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ኢትዮ ቴሌኮም እነዚህን አገልግሎቶች ለማስጀመር ከአንድ ዓመት በላይ የዘገየበትን ምክንያት ሲያስረዱ “የተሰጠን ፍቃድ እሱን አልፈቀደልንም ነበር። ስለዚህ በቴሌ ብር ሌሎቹን አገልግሎቶች እየሰጠን ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ለማግኘት ሥራዎችን ስንሰራ ቆይተናል” ብለዋል። 

ለመሆኑ አገልግሎቶቹ ምንድን ናቸው?

የቴሌብር ቁጠባና ብድር

በቴሌብር አማካኝነት በቅርቡ የተጀመሩት ሦስት አገልግሎቶች ተጠቃሚዎች ያለዋስትና/ማስያዣ እንዲበደሩ ወይም እንዲቆጥቡ የሚያስችሉ መሆናቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

  • ሳንዱቅ

ይህ የቴሌብር አገልግሎት ደንበኞች ገንዘብ የሚቆጥቡበት ሲሆን፣ ለተቀማጭ ገንዘብ ወለድ የሚከፈልበትን እና ከወለድ ነጻ የሆነ አመራጮችን አካቷል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ፣ ወለድ የሚከፈልበት ቁጠባ በየቀኑ የሚሰላ እና ደንበኞች በቀን ያገኙትን መጠን የሚያመላክት ነው።

  • እንደ ኪሴ

የቴሌብር ደንበኞች ግብይት እየፈጸሙ ገንዘብ በሚያንሳቸው ጊዜ ቀሪውን ገንዘብ የሚያገኙት ሥርዓት ደግሞ እንደኪሴ ይሰኛል። 

እንደኪሴ ደንበኞች ለግብይት ከሚያጥራቸው ገንዘብ በተጨማሪ እንደ የኤሌክትሪክ እና ውሃ ያሉ የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመፈጸምም ያስችላል።

ይህ አሰራር ደንበኞች ለክፍያ የጎደላቸውን እስከ 2 ሺህ ብር የሚሸፍንም ነው።  

  • መላ

ቴሌብር መላ፣ ደንበኞች የብድር አገልግሎት የሚያገኙበት መንገድ ሲሆን ግለሰቦችን እና የንግድ ተቋማትን የሚያካትት ነው።

በቴሌብር መላ ግለሰቦች በወር እስከ 10 ሺህ ብር፣ የንግድ ተቋማት ደግሞ እስከ 100 ሺህ መበደር እንደሚችሉ የሚያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ግለሰቦች የተበደሩትን በቀን፣ በሳምንት እና በወር መመለስ የሚችሉበትን አሰራር ማቀፉን ጠቅሰዋል።

ለንግድ ተቋማት ደግሞ ለግለሰቦች ከተጠቀሰው የጊዜ ገደብ በተጨማሪ የ3፣ የ6 እና የ9 ወር የሚመልሱበትን አሰራር አካትቷል።

ቴሌብር መላ “ለሥራ ማስኬጃ እንዲሁም አዳዲስ ሃሳብ ኖሯቸው ወደ ንግድ መግባት ለሚፈልጉ ሰዎችን ታሳቢ አድርጎ የቀረበ ነው። ለዚያ ነው በፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ያልሆነውን ማኅበረሰብ፣ ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ አቅም ይሆናል ብለን ያሰብነው” ሲሉም አክለዋል።   

መላ፣ እንደ ኪሴ እና ሰንዱቅ በተሰኙት የቴሌብር አገልግሎቶች በመጀመሪያ ዓመት ውስጥ በየወሩ በአማካኝ ከ3 እስከ 4 ሚሊዮን ደንበኞችን ለማገልገል እና ከ19.5 እስከ 20 ቢሊዮን ብር ለማንቀሳቀስ ማቀዱን ኃላፊዋ ጠቅሰዋል።

ከዚህም ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የብድር አገልግሎቱ ወይም ቴሌብር መላ ሲሆን 9.8 ቢሊዮን ብር ይሸፍናል።

6.4 ቢሊዮን ብር ክፍያን ለማጠናቀቅ ወይም እንደ ኪሴ ለተባለው አገልግሎት እንዲሁም 3.3 ቢሊዮን ብር ደግሞ በቁጠባ ወይም ሳንዱቅ በተሰኘው አገልግሎት የሚጠቃለል ነው።

ደጋግመው ብድር የሚወስዱ ደንበኞችን ጨምሮ በዓመት 108 ሚሊዮን ደንበኞችን ለማገልገል ማታቀዱንም አስረድተዋል።

አገልግሎቶቹ በተጀመሩ በቀናት ውስጥ የዕለት ብድር ወስደው የሚመልሱ እንዲሁም የሚቆጥቡ ደንበኞች መኖራቸውን ያነሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተስፋ ሰጪ እና “አስገራሚ” ሁኔታዎች መኖራቸው ገልጸዋል።

በቴሌብር መላ የሚሰጠው ብድር በሙሉ ዋስትና ወይም ማስያዣ እንደማይጠየቅበትም ጨምረው አስረድተዋል።