News today, Politics

ላቲቪያ ሩሲያን በሽብርተኝነት ፈረጀች

ሌላኛዋ የሩሲያ ጎረቤት ኢስቶኒያ ድንበሯን ለሞስኮ ዝግ አድርጋለች

የላቲቪያ ፓርላማ

ላቲቪያ ሌሎች የአውቶፓ ሀገራት ሩሲያ ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቃለች

የቀድሞ የሶቪየት ህብረት አንድ አካል የነበረችው እና የምስራቅ አውሮፓዋ ላቲቪያ ሩሲያን በሽብርተኝነት ፈርጃለች።

የሀገሪቱ ፓርላማ ዛሬ እንደወሰነው ከሆነ በፕሬዝዳንት ፑቲን የሚመራው የሩሲያ መንግስትን በሽብርተኝነት ፈርጇል።

ከሁለት ሚሊዮን ያልበለጠ ህዝብ ብዛት ያላት ላቲቪያ የሩሲያ እና ቤላሩስ ዜግነት ያላቸው መንገደኞች በአውሮፓ ሀገራት እንዲዘዋወሩ የሚፈቅደው የሸንገን ቪዛን እንዳይጠቀሙም እገዳ መጣሏን ሮይተርስ ዘግቧል።

ሩሲያ በዩክሬን ዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያደረሰች ነው በሚል የምትከሰው ላቲቪያ ሁሉም የአውሮፓ ሀገራት በሩሲያ ላይ ተመሳሳይ ማዕቀብ እንዲጥሉ ጥሪ አቅርባለች።

ሌላኛዋ የቀድሞ የሶቪየት ህብረት አንድ አካል የነበረችው ኢስቶኒያ ድንበሯን ለሩሲያ ዜጎች የዘጋች ሲሆን ምክንያቷ ደግሞ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ እና በዜጎቿ ላይ ስቃይ እያደረሰች ነው በሚል ነው።

ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ነበር ከስድስት ወራት በፊት ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት የገቡት።

በዚህ ጦርነት ምክንያት የዓለም የምግብ እና ነዳጅ ዋጋ ያሻቀበ ሲሆን ከ10 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገራት መሰደዳቸውን ተመድ ከሰሞኑ ሪፖርት ማድረጉ ይታወሳል።