
ከ 3 ሰአት በፊት
መሳሪያ ታጥቆ ከቁጠባ ሂሳቡ ገንዘቡ እንዲሰጠው ያስገደደው የሊባኖስ ዜጋ በሕዝቡ ጀግና ተብሎ ተወደሰ።
ሊባኖስ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ባንኮች ደንበኞቻቸው ወጪ በሚያደርጉት ገንዘብ ላይ ገደብ ጥላለች።
ይህ ግለሰብ ግን መሳሪያ ታጥቆና ባንክ ውስጥ ነዳጅ አርከፍክፎ ለሆስፒታል ክፍያ ለመፈጸም የሚያስፈልገው ገንዘቡ እንዲሰጠው በኃይል መጠየቁን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
በግለሰቡ እና በባንኩ መካከል ለስድስት ሰዓታት ከቆየ ፍጥጫ በኋላ ግለሰቡ የጠየቀውን ገንዘብ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስ ማግኘት ችሏል።
ይህ በስም ያልተጠቀው ግለሰብ ተግባርም በሕዝቡ ዘንድ አድናቆትን አስገኝቶለታል። ከባንኩ ውጪ ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች “ጀግና ነህ” እያሉ ጠርተውታል።
የግለሰቡ ወንድም ለጋዜጠኞች ሲናገር፤ “ወንድሜ በባንክ ሂሳቡ 210ሺህ ዶላር አለው። የሆስፒታል ወጪውን ለመሸፈን 5ሺህ 500 ዶላር ፈልጎ ነበር” ብሏል።
ከባንኩ ውጪ የነበሩት የግለሰቡ ወንድም እና ባለቤት፤ “ሁሉም ሰው ሊያደርገው የሚገባው ይሄን ነው። የራሳቸው የሆነውን ማግኘት አለባቸው” ብለዋል።
ኤልቢሲ የተሰኘ የቴሌቪዥን ጣቢያ የግለሰቡ ቤተሰብ አባላት በሆስፒታል እንደሚገኙ እና ገንዘብ እጅጉን ያስፈልጋቸው እንደነበር ዘግቧል።
የቴሌቪዥን ጣቢያው ጨምሮ እንደዘገበው ወደ ባንኩ በኃይል ከገባው ግለሰብ ጋር ድርድር ከተደረገ በኋላ ከቁጠባ ሂሳቡ 35ሺህ ዶላር ተሰጥቶታል።
ፖሊስ ግለሰቡን እና በእገታ ስር የቆዩ የባንክ ሠራተኞችን ከአካባቢው ይዞ የወጣ ሲሆን በግለሰቡ ላይ ክስ ይመሰረት እንደሆነ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
እአአ 2019 ላይ ሊባኖስ የገጠማትን ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ለመቋቋም ያስችለኛል ብላ ተግባራዊ ካደረገቻቸው ውሳኔዎች መካከል ሰዎች ከቁጠባ ሂሳባቸው ወጪ በሚያደርጉት የገንዘብ መጠን ላይ ገደብ መጣል ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ከአገር ውጪ በሚላክ የገንዘብ መጠን ላይም ገደብ ተጥሏል። ይሁን እንጂ እነዚህ ክልከላዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
በሊባኖስ የተከሰተው ምጣሄ ሃብታዊ ቀውስ የአገሪቱ ገንዘብ ዋጋውን ከ90 በመቶ በላይ እንዲያጣ አድርጎታል።
የዋጋ ግሽበት ጣሪያ ነክቷል፤ እንደ መድሃኒት እና ስንዴ ባሉ ምርቶች ላይ እጥረት አጋጥሟል። የተባበሩት መንግሥታት ከአምስት ሊባኖሳዊያን አራቱ በድኅነት ውስጥ ይኖራሉ ይላል።
