News today, Politics, social life

የፌደራል መንግስት እና የህወሓት የድርድር ሂደት ይሳካ ይሆን…?


ምሁራኑ “ህወሓት አሁን ላይ ድርድሩን የጠየቀበት ምክንያት ተገዶ ይሆናል፤ ምክንያት ፈልጎ ሊያቋርጠው እንደሚችል ግምታቸውን አሰቀምጠዋል
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ማጥቃቱን ተከትሎ ነበር በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተጀመረው።


ይህ ጦርነት ላለፉት 23 ወራት የዘለቀ ሲሆን ጦርነቱን ለማስቆም አሊያም ለማሸማገል ራሱ የፌደራል መንግስትን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት የአዉሮፓ ህብረት የተባሩት መንግስታት ድርጅት እና የተለያዩ አካላት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ድርድሩ እስካሁን ሳይሳካ ቀርቷል።


የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ድርድር ተስፋ እና ስጋቶች
መንግስት ከህወሃት ጋር ድርድር የሚካሄድበትን ቦታ ለመወሰን ከአፍሪካ ህብረት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አስታወቀ
አሁንም ጦርነት ለማስቆምና እልባት ለመፈለግ እየተደረገ ያለው ጥረት በህወሓት በኩል እንቅፋት እየገጠመው ነዉ ሲል መንግስት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።


መንግስት የሰላም ድርድሩን በአስቸኳይ ለመጀመር የሚያስችል የሰላም ምክረ- ሃሳብን የያዘ ሰነድ ማዘጋጀቱን ይፋ ቢያደርግም፣ ህውሓት በተቃራኒው ከፌደራል መንግስት ጥቃት እንደተከፈተበት በመግለጽ የተኩስ አቁም ስምምነቱ መፍረሱን ገልጾ ነበር።


የፌደራል መንግስትም ህወሓት ከነሀሴ 18 2014 አ.ም ጀምሮ በራያ፣ ወልቃይት ፣ ሰቆጣ እና አፋር ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።


ከተጠቀሰው ዕለት ጀምሮም በበትግራይ ክልል እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች እንዲሁም በኢትዮ ሱዳን ድንበር አካባቢዎች ላይ ጦርነቱ መቀጠሉ የተገለጸ ሲሆን፤ ህወሓት የዘመን መለወጫ ዕለት ማለትም መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣዉ መግለጫ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ለመወያየት እና ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መዘጋጀቱን አስታውቋል።


ፃድቃን ገብረተንሳይና ጌታቸው ረዳን ያካተተ ከፌደራል መንግስት ጋር ለሚደረገው ድርድር የሚወክሉትን ቡድን ያፈ ያደረገው ህወሓት አለማቀፉ ማኅበረሰብ በታዛቢነትና ድጋፍ በማድረግ እንዲሳተፉ እንደሚፈልግም ገልጿል።


የህወሃትን የእደራደራለሁ መግለጫን ተከትሎ ብዙዎች ተስፋ እና ስጋትን እንደተሰማቸው በተለያዩ መንገዶች ሃሳባቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
አል ዐይን አማርኛ የህወሓት ለመደራደር ዝግጁ ነኝ ማለቱን ተከትሎ ስለጉዳዩ ምሁራንን አነጋግሯል።


አቶ አበበ ይርጋ በባህር ዳር ዩንቨርሲቲ ስር ባለው የብሉናይል ውሀ ኢንስቲትዩት የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ጥናት መምህር ናቸው፤ የህወሃትን በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ከፌደራል መንግስት ጋር እደራደራለሁ ማለቱን እንዴት ያዩታል? በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ፤
“ህወሀት ወደ ድርድር እንዲመጣ ለረጅም ጊዜ ሲለመን ነበር፣ ነገር ግን ቅድመ ሁኔታ ሲደርድር እና ሰላም እንዳይፈጠር የቻለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል።

በድንገት ያለ ቅድመ ሁኔታ በየትኛውም ቦታ እደራደራለሁ ማለቱ ከልቡ አይመስለኝም፣ ይሄንን መግለጫም ያወጣው በሎጅስቲክስ እና ፕሮፓጋንዳ ሲያግዙት የቆዩት አካላት አዘውት ነው” ብዬ አስባለሁ ብለዋል።


“በኢትዮጵያ የተለየ ፍላጎት ያላቸው ሀገራት ቁጥራቸው እየጨመረ ነው” የሚሉት መምህር አበበ “ህወሓት እየተሸነፈ ሲመስላቸው እና ተጨማሪ ድጋፍ ለማሰባሰብ እንዲያመቻቸው” ለድርድር ዝግጁ መሆኑን እንዲያሳውቅ ሳያደርገው እንዳልቀረ ግምት እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።


“ህወሓት እደራደራለሁ ማለቱ በፌደራል መንግስት ላይ በሚደረግ ጫና ምክንያት መከላከያ ሰራዊት ማጥቃቱን ትቶ አሁን ባለበት ቦታ እንዲቆም ቀስ በቀስም ለአራተኛ ዙር ጦርነት የመዘጋጃ ጊዜ እንደሚያገኝ በማሰቡ ሊሆን ይችላል” ሲሉም ተናግረዋል።


“ድርድሩ የውጭ ጣልቃ ገብነት የተጫነው ይመስላል” የሚሉት መምህር አበበ “ለኢትዮጵያ ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣላት ከድርድሩ ጎን ለጎን በህወሀት ጥቃት እየደረሰበት ያለውን የትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ህዝብን መታደግ ሲቻል እና መንግስታዊ አገልግሎቶችን መጀመር ብቻ” እንደሆነ ጠቁመዋል።


ሌላኛው በድርድሩ ዙሪያ አል ዐይን አማርኛ ያናገራቸው በጅግጅጋ ዩንቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ህግ መምህሩ ሰለሞን ጓዴ ናቸው።


እሳቸው እንዳሉት “በእኔ አመለካከት “ህወሓት አሁን ላይ ድርድሩን የጠየቀበት ምክንያት ተገዶ ይሆናል የሚል እሳቤ አለኝ ምክንያቱም ይፈልጉት የነበረዉ ስትራቴጂካዊ ቦታ ተይዞባቸዋል በዚህም ጫናዉ ሲበዛባቸዉና የጦርነት የበላይነትን ሲያጡ መጀመሪያ አጎንብሶ ከዛም አፈር ልሶ ለመነሳት የሚደረግ ሙከራ ነዉ ብዬ ነዉ የማምነዉ በአንድ ሳምንት ዉስጥ ሽንፈት ካልሆነ በስተቀር ሊፈጠር የሚችል አሳማኝ ምክንያት የለም” ሲሉ ገልጸዋል፡፡


“ህወሓት እንዳለው ወደ ድርድር ከመጣ የታጣቂዎቹ ትጥቅ መፍታት ጉዳይ የድርድሩ ዋነኛ ጉዳይ ይሆናል” የሚሉት መምህር ሰለሞን “ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ መተማመንን የሚያጎለብት ስራ መሰራት አለበት” ብለዋል፡፡


ድርድሩ ፍሬያማ እንዲሆን ከተፈለገ መጀመሪያ ሰላማዊ የሆነ አየር ያስፈልጋል፤ ሉዓላዊነት መከበር አለበት፣ ይህ የሚሆነው ደግሞ የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ ሲፈቱ እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ዳር ድንበር መቆጣጠር በሚያስችለው መንገድ ሲሰማራ ብቻ እንደሆነም መምህር ሰለሞን አክለዋል።


መምህር ሰለሞን አክለውም የህወሓት የእስካሁኑ የፖለቲካ ባህል ምን ጊዜም እራሱን ብቻ የሚያስቀድም በመሆኑ እደራደራለሁ ማለቱ ከልቡ ሊሆን እንደማይችል ተናግረዋል።


በመንግስትና ህወሓት መካከል የሚደረገው ድርድር ሁሉንም ያሳተፈ ኢንዲሆን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት ጠየቀ
“ህወሓት እኔ ያልመራሁት ነገር አይደረግም የሚል ድርቅ ያለ መንገድን የሚከተል ድርጅት ነው” የሚሉት መምህር ሰለሞን ድርድር በባህሪው ሰጥቶ መቀበልን እና ሰላማዊ ሁኔታዎችን የሚፈልግ በመሆኑ ድርድሩ የመሳካት እድሉ ጠባብ መሆኑን ጠቁመዋል።


ህወሓት ድርድሩን ቢጀምረው እንኳን ምክንያት ፈልጎ ሊያቋርጠው እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀመጡት መምህር ሰለሞን የፌደራል መንግስት በህወሀት ወጥመድ ሊገባ እንደማይገባም አሳስበዋል።


የፌደራል መንግስት ከዚህ በፊት ባወጣው መግለጫ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ከህወሃት ጋር በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ እንደሚደራደር ማሳወቁ ይታወሳል።


ለዚህ ድርድርም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ አብይ ኮሚቴ መቋቋሙን እና ሌሎች ንዑስ ኮሚቴዎችም ተቋቁመው ስራ መጀመራቸው መገለጹ አይዘነጋም።