News today, Politics

የአሜሪካ ፖሊስ የዶናልድ ትራምፕን መኖሪያ ቤትን ፈተሸ


የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ቤት በኤፍ ቢ አይ ተፈተሸ

የአሜሪካ ፖሊስ የቀድሞውን የሃገሪቱን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መኖሪያ ቤትን በርብረዋል፡፡

በፍሎሪዳ የሚገኘውን የትራምፕን መኖሪያ የፈተሸው የፌዴራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍ.ቢ.አይ) መሆኑን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡

ፍተሻው ዶናልድ ትራምፕ ምናልባትም በደጋፊዎቻቸው ከተፈጸመው የካፒቶል ሂል ጥቃት ጋር በተያያዘ ከቤተ መንግስት ያሸሹት ሚስጥራዊ ሰነድ ይኖር ይሆን በሚል የተካሄደ ነው መሆኑን ሲ.ኤን.ኤን ዘግቧል፡፡

ትራምፕ ኒውዮርክ በሚገኘው ህንጻቸው ላይ ሳሉ ነው መኖሪያቸው የተፈተሸው።

“ማር-ኤ-ላጎ የሚገኘው ቅንጡ መኖሪያ ተከቦ ነው የሚገኘው፤ በብዙ የኤፍ.ቢ.አይ ፖሊሶች ተወርሮም ይገኛል” ሲሉ ዶናልድ ትራምፕ ሶሻል ትሩዝ በተሰኘ ማህበራዊ ሚዲያቸው አስታውቀዋል።

በቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ (2024) እንዳይወዳደሩ ለማድረግ በማሰብ የተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ዶናልድ ትራምፕ በፈረንጆቹ 2024 ለሚካሄደው ምርጫ ለመወዳደር ያላቸውን ፍላጎት በይፋ ባይገልጹም፣ ባለፉት ጥዊት ወራት ለመወዳደር ፍላጎት እንዳላቸው ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

ትራምፕ ከካፒቶል ሂሉ ጥቃት እንዲሁም የተሸነፉበትን የምርጫ 2020ን ውጤት በኃይል ለመቀየር ሞክረዋል፤ ሌሎች ሚስጥራዊ ሰነዶችንም አሽሽተዋል ከመባሉ ጋር በተያያዘ በምርመራ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።